ለማህበረሰቡ የሚሰጡ ዘመናዊ አገልግሎቶችን በተሞክሮ በመቀመር ማስፋት እንደሚገባ ተገለፀ
04 ግንቦት 2018
ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማገዝ ችግር ፈቺ እንዲሆኑ በማስቻል እረገድ በርካታ ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ የሚገኝ ሲሆን ከተከናወኑት ተግባራት ውስጥ ለሌሎች ተቋማት በተሞክሮነት ለማስፋት የሚያስችሉ ሲስተሞችን የመለየትና የማስፋት ስራ ይከናወናል፡፡
በተለይም ከተገልጋዩ ማህበረሰብ የአገልግሎት ፍላጎት ጋር ቀጥተኛ ተዛማጅነት ያላቸውን ተግባራት በመለየት በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማምጣት አዳዲስ እና የተሻሻሉ የአገልገሎት ሲስተሞችን በማልማት ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡
በዚህም መሰረት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ የምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ፅ/ቤት ለምቶ የተዘጋጀ የምግብና መድሀኒት ክላስተር ሲስተም ከክ/ከተማው የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ፅ/ቤት ጋር በመቀናጀት ወደ ተግባር በማስገባት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የክ/ከተማው ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ መስከረም ሙለታ ለተሞክሮ በቀረበው ሲስተም ግምገማ በተደረገበት ወቅት ገልፀዋል፡፡
የምግብና መድሀኒት ክላስተር ሲስተም በዋናነት ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ቅድመ ሁኔታን ጨምሮ በጽ/ቤቱ የሚሰጠውን የብቃት ማረጋገጫ አገልገሎት እና መሰል አገልግሎቶችን በኦንላይን መጠየቅ የሚያስችል የተገልጋይ መመላለስን የሚቀንስ እና በቁጥጥር ስርአቶን ወቅት የተገልጋይ ተቋማት መብትና ግዴታን በግልፅ የሚያመላክት መሆኑ ተገልጿል።
በተለይም ተገልጋይ ተቋማት የመብት ጥሰት እንዳይፈፅሙ ከመመሪያና ከደንብ እንዲሁም ከአከባቢ ምቹነት አንፃር ያሉ ድንጋጌዎች ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ መረጃዎች በዌብሳይቱ ተካተው መቅረባቸው ተገልጿል።
በቀረበው የአገልግሎት መስጫ ሲስተም ላይ አስተያየት የሰጡት በቢሮ የአገልግሎት አሰጣጥ ክትትልና ድጋፍ ባለሙያዎች በሰጡት አስተያየት ክ/ከተማው በራስ ተነሳሽነት የሚሰጡ አገልግሎቶች ለማዘመን ከፅ/ቤቶች ጋር በመቀናጀት ያለማቸው ሲስተሞች ችግር ፈቺና በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ እሴት የሚጨምሩ መሆናቸውን ገልፀው ማሻሻያ ያስፈልጋቸዋል ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ሰጥተዋል።
በቀጣይም በተሰጡት ሀሳቦች ላይ ማስተተካከያ በማድረግ የምርጥ ተሞክሮውን ለሌሎች የማስፋት ስራ እንደሚከናወን ተመልክቷል።